
” ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።” (ዮሐ.3:6)
***************************************
” እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍ.1:27)
ብዙዎች ቤተ እምነቶች በኒቅያ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት አጥራቸውን ከልለው “ለሽ ብለው ” ተኝተዋል ። ሌሎች አጥራቸውን ከአጠሩት በመውጣት በተረዱት ለየት ያለ አስተምህሮት ሕዝቡን እስከተወሰ ይነዱትና እንደገና አስተምህሮታቸው ስህተት እንደሆነ በመናገር ንስሐ ይገባሉ ። ይህ የተለመደ ሆኖአል ። ሲጀመር በመንፈስ ቅዱስ ያልተረዱት ስለነበር ኃሳባቸውን ቢቀይሩ አይደንቅም ። እውነተኛ የቃሉ መገለጥ እያደገ ይሄዳል እንጂ ተሳስተን ነበር ብሎ ከዜሮ አይጀምርም ። በሌላ አገላለጥ ራሳቸውን የሚለውጡ “የብርሃን” መልክተኛ ናቸው ። የሚደንቀው ደግመው ደጋግመው ከዜሮ ሲጀምሩ አጀባቸውም ከእነሱ ጋር መጀመሩ ነው ።
ወደ ሰሞኑን መነጋገርያ አስተምህሮት ስንመጣ ደግሞ ” ሰው መንፈስ ” ነው ብሎ ሲያስተምር ከርሞ ሐሳቡን ቀየረ በተባለው ሰው አማካኝነት በነገረ ጉዳዩ ሐሳቤን ሳስቀምጥ ወንድሞችም እንደሚጨምሩበት ተስፋ በማድረግ ነው ።
እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና ምሳሌ እንደፈጠረው ክርክር የለውም ። ሰውና እንስሳት በአፈጣጠራቸው የሚመሳሰሉበት ከመሬት መገኘታቸው ሲሆን ፤ የሚለያዩበት ደግሞ ሰው ከእግዚአብሔር የእግዚአብሔርን የሕይወት መንፈስ በመካፈሉ ነው ። ሰው የእግዚአብሔርን ሕይወት በአካሉ ካልገለጠ እንደ እንሰሳ ነው ። ” ሰው ግን #ክቡር_ሆኖ_ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ።” (መዝ. 49:12) አረ! አንዳንዴም ደግሞ ከእንሰሳ አንሶ ይገኛል ።” በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም። ” (ኢሳ. 1:3)
ፊተኛው አዳም ሕያው ነፍስ ሆኖ መገለጡ የታመነ ነው ። ከመሬት አፈር በተበጀው አካሉ ውስጥ የሕይወት መንፈስን ቢቀበልም እነደ እንሰሳ ሕያው ነፍስ መሆኑ የእግዚአብሔርን መልክ መግለጥ አልቻለም ። ለምን የሚል ቢኖር ይህን ጨምሮ ያንብብ ፦ ” እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ … (1ኛ ጢሞ. 3:16)
ምሥጢሩ ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው ። የምኑ ምሥጢር ? እግዚአብሔር ን የመምሰል ነዋ! ሰው በእግዚአብሔር ምሳሌ እኮ ነው የተፈጠረው ። የእግዚአብሔር ምሳሌ ደግሞ በሥጋ መገለጥ አለበት ። ስለዚህም የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ሥጋችን ሳይሆን በሥጋችን የሚገለጠው የሕይወት መንፈስ ነው ። በኢየሱስ የሆነው ይኸው ነው ። በፊተኛው አዳም ያልሆነው በኃለኛው አዳም ሆነ ። ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ ።
#Joseph_Demissie( የሕይወት ቅመም 106) በቅርቡ ፖስት ካደረገው ቀንጭቤ በመስማማት ላቅርበው ።
” እግዚአብሔር ልጆችን የወለደው ሕብረትና ተልዕኮ ፈልጎ ሳይሆን ራሱን በልጆቹ ውስጥ ማየት ፈልጎ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የእግዚአብሔር አይነት ነው። እግዚአብሔር የሚወልደው የራሱን አይነት ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ሕይወት የአባታቸው ሕይወት አይነት ነው። በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር ልጆች መካከል ምንም አይነት የባሕርይ ልዩነት የለም። አባት ያለውን ሁሉ ልጅ አለው። አባት የሌለውን ልጅ የለውም፣ ሊኖረውም አይችልም፣ ከየትም አያመጣም።
” እግዚአብሔር ስለ እኛ ምን ያስባል? ምንስ ያውቃል? እግዚአብሔር ልጆቹ እንደሆን፣ ማንነቱ ማንነታችን፣ ባሕርይው ባሕርያችን፣ እኛ በእርሱ እርሱም በእኛ ውስጥ እንዳለ ነው የሚያስበውና የሚያውቀው።…እንደ ማንነታችን መኖር ያልቻልነው ራሳችንን ያወቅነው እግዚአብሔር እንደሚያውቀን ሳይሆን ከሥጋ ተነስተን ስለሆነ ነው። …። እግዚአብሔር የሚያውቀው ማንነታችን የእርሱ መልክ ያለው፣ እንደ እርሱ የሆነውንና እርሱን የሚመስለውን ነው።” ( እስከዚህ የተወሰደ)
እግዚአብሔር መንፈስ ነው ። እግዚአብሔር የዘላለም ሕይወት ነው… ። የዘላለም ሕይወት ከተሰጠን ፤ በማያሻማ መልኩ ሕይወቱን ተካፍለናል ። ስለዚህ የመለኮታዊው ባህርይ ተካፋይ ነን ማለት ነው ። ይህን ሕይወት በሥጋ እንገልጣለን ።
” ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።” (2ኛ ቆሮ. 5:1)
ድንኳን የተባለው ጊዚያዊ መኖርያችን የሆነው ሥጋችን ነው ። የዳንን ሁላችንም አዲሱ ሰው ነን ። አዲሱ ሰው የተባለው መንፈስ ነው ፤ በሥጋ ያድራል ።
ለዛሬ አበቃሁ! ንጋቱ መርዶ የማትሰሙበት ይሁንላችሁ ።
ሻሎም ሻሎም፦