
የእግዚአብሔር ፍርድ በብረት እና በእንጨት ቀንበር በህዝቦች ላይ
Brother Binyam T. Alemayehu 1/31/2018
የእ/ር ቃል መንፈሳዊ ሰይፍ ነው እኔን ጨርሶ ሌላውን ሊጨርስ መገላበጡ አይቀሬ ነው። የእ/ር ቃል የተባለው እየሱስ ክርስቶስ የቃሉ ሰይፍም እሱ ነው የህይወት ዛፉም እሱ ነው፡ እሱን የበላ ሁሉ ያድጋል። በሰይፉም ከእ/ር ያልሆነው ሁሉ ከእሱ ይለያል። ምንም እንካ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም ጠባብ መንገድ ላይ አዳም እንዳይገባ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ ቢቀመጥም ሰይፉ እኔነትን ሲቀላ ቢያምም፡ ግን አዲሱ ሰው ሳይጎዳ ሳይከለከል የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን አልፎ በክርስቶስ ለመግባት ድፍረት ለሰጠው ጌታ ክብር ይሁን። እንደምናስተውለው በአሁኑም ዘመን ጌታ በልጆቹ ብዙ እየተናገረን ነው።
የዛሬው አርእስት ስላነሳሳኝ እኔም አንድ ቃል ትዝ አለኝና ሰይፌን[ቃል] ከሰገባው መዘዝኩ [አደራ መንፈሳዊ ቋንቋ እያወራን እንዳለ ከግንዛቤ ይግባ] በብሉይ ኪዳን “መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 19/17 ከአዛሄልም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ። ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ ኤልሳዕ ይገድለዋል።” በአዲስ ኪዳን ‘የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል። ‘ዕብራውያን 4:12 ነውና ጥቂት ልበል።
በህዝቦች ታሪክ ስናስተውል ማንኛውም እግዚአብሔርን ያከበረ ህዝብ ታላቅ የተከበረ ህዝብ ሲሆን የናቁት ሲናቁ በአንድም በሌላ መንገድ በየፊናው ይስተዋላል። መጽሐፈ ምሳሌ 14/34 ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ ኃጢአት ግን ሕዝብን ታስነውራለች። Prov 14/34 Righteousness exalteth a nation: but sin is a reproach to any people.
እ/ር ቃል አለ ማለት ሆነ እንደ ሆነ እናውቃለን። የእ/ር ፕሬንስፕል ወይም መመርያ እንደ ምናስተውለው ህዝቦች በጽድቅ ሲሄዱ ከፍ ከፍ ይላሉ በኃጢአት ሲሄዱ ግን ሕዝብ ነውረኛ ይሆናል። እ/ር ህዝቦችን ሲፈርድ በሁለት ቀንበር የተመሰሉ ፍርዶችን በእነሱ ላይ ሲጠቀም እናያለን የመረረ ቁጣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሲሆን በብረት ቀንበር an iron yoke ውስጥ ያስገባቸዋል የለዘበ የተሻለው ፍርድ ደግም የእንጨት ቀንበር Wooden Yoke ያደርገዋል። ”በቀደሙት ላይ የሆነው ሁሉ ለትምርታችን ተፅፈዋልና“ ከዚህም የሚቀርል ነገር አለ።
ዘመናዊ ትራክተር በአገራችን ገና ስላልተዳረሰ ቀምበር ምን ማለት እንደሆነ ኢትዮጵያዊ ያውቃል። ቀንበር እንደ ምታውቁት ገበሬዎች በበሬ ለማረስ በአንገታቸው ላይ የሚያጠምዱት መጥመጃ ቀንበር ይባላል። በሬ የሰው ሰራተኛ ነው ስለዚህ በዚህ ሃሳብ ላይ ቀንበር በሰው ላይ የሚያመለክተው ተገዶ ተጠምዶ ወደ ሰራተኝነት ግዞት በእ/ር አልፎ መሰጠቱን ነው። እስራኤል የተመረጠ ስለሆነ ከእግዚአብሔር ፍርድ ያመልጣል ማለት አይደለም እንዳውም ፍርዱ ይብሳል። ‘ነገር ግን ይህን ሳያውቅ ቀርቶ መገረፍ የሚገባውን ያህል ያደረገ አገልጋይ በጥቂቱ ይገረፋል። ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራም ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል። ‘ ሉቃስ 12:48
እንደ ምናውቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ አይነት ፍርዶች እንዳሉ እናውቃለን በመንፈሳዊ ገጽታቸውም ሆነ በአካላዊም ማለት ነው። አለም የማያስተውለው የመጀመርያው ፍርድ በአማኞች ላይ ለ2000 አመታት ፍርዱ ከእ/ር ቤት ዘንድ ጀምሮ ይህ ፍርድ አሁንም እየተካየደ ነው። ብዙ ቁልፎችን ወደ መንግሥቱ መክፈቻ የተሰጠው ጴጥሮስ ይህንን ፍርድ ለእኛ ያስተዋውቀናል.
‘ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሶአልና። እንግዲህ ፍርድ የሚጀምረው በእኛ ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን? ‘1 ጴጥሮስ 4:17
ኦሪት ዘፍጥረት 18/25 …የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?
ወደ ዕብራውያን 12/23 … የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ …ደርሳችኋል።
በመጀመርያ በእርሱ በእግዚአብሔር ላይ የሚያምጽ ህዝብ ላይ እ/ር እንዴት እንደ ሚፈርድ እንየው። ‘በራብና በጥም፣ በእርዛትና በከፋ ድኽነት እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በ-ዐ-ን-ገ-ት-ህ ላ-ይ የ-ብ-ረ-ት ቀ-ን-በ-ር ይጭንብሃል። ‘ ዘዳግም 28:48 አዲሱ መደበኛ ትርጉም በሚቀጥለው ቁጥር ላይ የብረት ቀንበር ይጭንብሃል ማለቱ ምን ማለት እንደሆነ ፍቺውን ይሰጣል
‘ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአንዱ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ዳርቻ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይበትንሃል። በዚያ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። ‘ዘዳግም 28:64
ከቃሉ ስናስተውል እስራኤል በሃጥያቱ ሲቀጥልና ንስሃ አልገባም ሲል እግዚአብሔር ህዝቡን ለማጥፋና በምድር ላይ ለመበተን ቃል ሲገባ እናስተውላለን። የየብረት ቀንበር የመጨረሻው ስርአት ማስያዟ ፍርድ ነው። ይህም ማለት በህዝቦችና በከተማ ጥፋት ይሆናል ማለት ነው። ብዙ ሰዎችም ያለ ምህረት ይገደላሉ ማለት ነው። መራራ የሆነ የህዝቦች ፍልሰትና ስደትንም ክፉ ፈላጭ ቆራጭ የውጪ ገዝዎች ስር መውደቅንም ያካትታል። ይህ በአሦር ንጉሥ የሆነውን ማየት በቂነው እስራኤልን አጠፋ የቀሩትንም በግዞት ወሰዳቸው።”መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 17/6 በሆሴዕ በዘጠኝኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ወሰደ፥ እስራኤልንም ወደ አሦር አፈለሰ፥ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው።” ወሰዳቸው።” ተጨማሪ በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 17/18-23 ይመልከቱ።
ይህም ከአንድ ምእተ አመት ቡሃላ ባቢሎን እዮርሳሌምን አጥፍቶ የአይሁድ ህዝብን ለ70 አመት በግዞት ወሰዳቸው። ሰአቱ ሲደርስ እራሱ እግዚአብሔር ወደ ክብራቸው መለሳቸው።
በመጨረሻም በ70 A.D. ሮማውያን ታይተስ በተባለ ጀነራል እዮርሳሌምን አቃጠላት የግፉ ብዛት በአንድ ዛፍ ላይ ብዙሰዎችን ይሰቅሉ ነበር። የቀሩትንም አይሁድ ወደ ባርነት አጓዙ።
እንግዲህ እነኚህ እ/ር የቀጠራቸው የፍርድ ብይኑን ማለትም ፈቃዱን የብረት ቀንበር ጫኞች አርጎ ሃይል የሰጣቸው የግራ እጁ መአት መግለጫዎቹ መካከል ምሳሌዎች ናቸው። በህዝቦች ላይ በዚህ መልክ ፍርዱን እንዴት እደሚፈጽም ኮምፕሌክስ ውስብስብ አሰራሩን ማሳያም ናቸው። ከዚህ ለዘብ ያለው ፍርድ ግን ኤርሚያስ የእንጨት ቀንበር ያለው ነው ይለናል። በዘመነ መሳፍንት እስራኤልን ለሃጥያታቸው ቅጣት ህግ አልባ እየሆኑ ስላስቆጡት ከሃገራቸው ሳይወጡ ወራሪዎች በብርቱ እጅ እንዲገዙ ሲፈርድባቸው።
‘ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋር አብረው ኖሩ። እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔር አምላካቸውንም ረሱ፤ የበኣልንና የአስታሮትን አማልክት አመለኩ። እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኵስርስቴም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ ግን የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። ‘ መሳፍንት 3:5-9
Judg 3/8 Therefore the anger of the Lord was hot against Israel, and h-e s-o-l-d t-h-e-m into the hand of Chushan–rishathaim king of Mesopotamia: and the children of Israel served Chushan–rishathaim eight years.
እንደ ምናስተውለው ከ8 አመት ግዞት ነበር የብረት ቀንበር አልነበረም ቡሃላ ኤርሚያስ እንደ ሚገልፀው የእንጨት ቀንበር ነበር። ነብዩ ኤርሚያስ ለህዝቡ ሲናገር ይሁዳና እዮርሳሌም ያለማቃረጥ የመለኮትን ህግ ላይ ሃይለኝነትን ስላሳዩ ጌታ የሰለሞንን መቅደስ እደሚተውውና እደሚያጠፋው ነገራቸው።
”እዩ። እነዚህን ሁሉ ስታደርጉ፣ ይላል እግዚአብሔር ፤ ደጋግሜ ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁኝም፤ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን አልመለሳችሁም። ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ አሁንም ስሜ በተጠራበት ቦታ፣ በታመናችሁበት ቤተ መቅደስ፣ ለአባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁት በዚህ ስፍራ እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን፣ የኤፍሬምን ሁሉ ሕዝብ እንዳስወገድሁ፣ እናንተንም ከፊቴ እጥላችኋለሁ።’ “እንግዲህ ስለማልሰማህ፣ ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን፤ አትማልድላቸውም። ‘ኤርምያስ 7:12-16”
እንደ ምናስተውለው ኤርምያስ ይህን ቃል ሲቀበል በመንፈሳዊው አለም እ/ር ብይኑን ስለ ሰጠ የማይመለስ ነውና ለህዝቡ እንዳትፀልይ አልሰማህምና ሲለው እናስተውላለን። ይሄኛው ደግሞ ጫን ያለው መጣ ነው ለንስሃ እንኳ እድል ፈንታ የሌለበት ፍርድ ነበር።
ኤርምያስ መፀለይ የሚችለው ፍርዱ እንዲቀል እንጂ እንዲ ሰረዝ መፀለይ አይችልም። ኤርምያስ 23-30 ህዝቡ ለእግዚአብሄር ብይን በሰላም ተቀብለው ከተገዙ በምድራቸው በእንጨት ቀንበር እንዲቆዩ እንደ ሚፈቅድላቸው ነገራቸው። ብይኑን ከታቃወሙ ግን እግዚአብሔር በብረት ቀምበር ሆነው ወደ ባቢሎን በግዞት እንደ ሚሄዱ ነገራቸው።
‘እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “የዕንጨት ቀንበር ሠርተህ በጠፍር ማነቆ አያይዘውና በዐንገትህ አስገባው፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት ሰዎች በኩል ለኤዶም፣ ለሞዓብ፣ ለአሞን፣ ለጢሮስና ለሲዶና ነገሥታት መልእክት ላክ። ‘ኤርምያስ 27:2-3
ይህ መልክት ለአይሁድ ንጉስ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገሮችም ጭር ለናቡክነዶፀር ተሰጥተው ነበር፡ ሁሉም ህዝቦች ለእንጨት ቀምበሩ እንዲገዙ እ/ር አዞ ነበርና።
‘በታላቁ ኀይሌና በተዘረጋው ክንዴ ምድርን፣ በላይዋ የሚኖሩትን ሰዎችና እንስሳት ፈጥሬአለሁ፤ ለምወደውም እሰጣለሁ። አሁንም እነዚህን አገሮች ሁሉ ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ የዱር አራዊት እንኳ እንዲገዙለት አደርጋለሁ። የእርሱ አገር በተራው ለሌሎች እስከሚገዛበት ጊዜ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ለእርሱ፣ ለልጁና ለልጅ ልጁ ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜ ብዙ ሕዝቦችና ታላላቅ ነገሥታት እርሱን ይገዙታል። ‘ኤርምያስ 27:5-7
አስተዋላችሁ “በታላቁ ኀይሌና በተዘረጋው ክንዴ ምድርን፣ በላይዋ የሚኖሩትን ሰዎችና እንስሳት ፈጥሬአለሁ፤ …. አሁንም እነዚህን አገሮች ሁሉ ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ king of Babylon, Nebuchadnezzar, “My servant.” ” በሌላ አነጋገር ይህን ሁሉ ምንም እንኳ የአህዛብ ንጉስ ቢሆንም የኔ ሰራተኛ አገልጋየ የፍርዴ አስፈፃሚ ነው። ”ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤“
ተመልከቱ የእ/ርን አሰራር ሳይቃወም ለተገዛ የባሰ መከራ አላመጣበትም ሲል እንይ። ‘ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዐንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚያገለግለውን ማንኛውንም ሕዝብ በገዛ ምድሩ እንዲቀርና እያረሰም በዚያ እንዲኖር አደርገዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር ።” ኤርምያስ 27:11
ቡሃላም ኤርሚያስን የእንጨት ቀምበር አድርጎ በህዝቡ መካከል እንዲ ዘዋወርና የእ/ር ፍርድን እንዲያስረዳ ተነግሮት አደረገው ሌላ ነብይ ሃናንያ የተባለ በእ/ር ብይን ስላልተስማማ ተሰናከለበትና የእንጨቱን ቀምበሩን አውልቆ ሰበረው።
‘ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ ዐንገት ወስዶ ሰበረው፤ ‘ኤርምያስ 28:10 ኤርሚያስ ምንም አልመለሰለትም ነብይ ስለሆነ ህዝቡ ሁሉ በልባቸው ጣኦት ስለሚመሩ ለጌታ ፍርድ እንደማይገዙ የነሱም ልቦና በጌታ ፊት ተመሳሳይ እንደሆነ ያውቅ ነበረና። በናብክደኖፆር ለመገዛት ሃሳቡም የላቸውም ነበርና ምክንያቱም ጌታ የነሱ ማልያ ለብሶ እንደ ሚጫወት፡ያስቡ ነበርና። ትንቢተ ኤርምያስ 2/35 አንቺ ግን[ይሁዳ]፦ ንጹሕ ነኝ በእውነት ቍጣው ከእኔ ተመልሶአል አልሽ። እነሆ፦ ኃጢአት አልሠራሁም ብለሻልና በፍርድ እከስስሻለሁ።“
ይህንን ውብ ቤተ መቅደስ ጌታ ያፈርሰዋል ብለው አላመኑምና መራራ ተቃውሞ ተቃወሙ። ትንቢተ ኤርምያስ 7/4 የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ ይህ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ።
እደ ምናስተውለው ጌታ ሁለት ነብያትን አስነሳና ኤርሚያስና ሃናንያ በልባቸው አመጽ የተሞሉት በደመነፍስ ሃናንያን ተከተሉ በአመጽ ቲዮሎጂ የሚያምኑት በናቡክኖዶፆር ላይ አመፁ ሳያውቁት እ/ር ላይ እንዳመፁ ግን ገና አላስተዋሉም ነበር።
ኤርሚያስን የተከተሉት ጌታ ህጉን ወደጎን ያስቀመጡትን እንደ ሚፈርድባቸው ስለሚያቁ በፈቃዳቸው ለእንጨት ቀንበሩ ተገዙ። አብዛኛዎቹ ግን ጌታ ባርያ እንዲሆኑ ፈቃዱም ፍርዱም አይደለም ያሉ ሁሉ ሰይፍ አነሱና በሰይፍ ጠፉ ሁሉም አንድም ሳይቀር ተዋጉና ሁሉም በሰይፍ ወደቁ። በነሱ ምክንያትም ከተማው መቅደሱ አገሩ ሁሉ ጥፋት ሆነበት። ለቀንበሩ ያልተዋጉ ሁሉ ግን በባቢሎን ምርኮ 70 አመት አሳልፈው ተባዝተው ተመለሱ። እንህን የመሰሉ ብዙ ልናይ ብንችልም ይህ ለምሳሌ ያህል በቂ ነው።
መቸም የእግዚአብሔር የመንፈስ ሰዓቱን ለማስተዋል ብትሞክሩ ሁሉ ነገር አሁን ሆኖ ታገኙታላችሁ ጊዜ ያለው ከመንፈስ በታች ብቻ ነውና። አንድ ወንድም ድሮ የነገረኝ ትዝ አለኝ አንድ የእ/ር ልጅ ጌታ በራእይ እንዲረዳው ፈጣን መልአክ ይልክለትና ያሳየዋል በጣም ተገርሞ መላኩን ለመሆኑ መቼ ተፈጠርክ ብሎ ይጠይቀዋል መላኩም አሁን አሁን ሉኡሉ ቃል ሲያወጣ ቃሉን ለማስፈፀም ተከሰትኩ አለው።
ከሰማይ ባታች በጊዜ ለተወሰነው ግዛት ግን ሰዓቱ ያለማቋረጥ ወደፊት በመቁጠር ላይ ነው። የእግዚአብሔር ልጆችም በክርስቶስ ክብር ማለትም በእግዚአብሔር ክብር ፍፁም መልክ መገለጥ የሚታዩበት ጊዜን፡ ከዘመን ጅማሬ ጀምሮ ፍጥረታት ሁሉ ከመበስበስ ባርነት ግዛት ሆነው በውን እስኪያያቸው በሲቃና በምጥ ሲናፍቁ ቆይተዋል። በቅርቡም ለቅሳቸውና ሲቃቸው በቅርብ በእግዚአብሔር ልጆች በክርስቶስ ክብር መልስ ያገኛል።
አሁን የእግዚአብሔር ልጆች በአለም ላይ እየባሰ በመጣው ክፋት ሊከፋቸው ወይም ሊደሰቱ አይገባም የነገሮች እውነተኛ ተፈጥሮ ስለ ሚያስተውሉ የሚያስገርማቸው የእግዚአብሔር ረቂቅ አሰራሩ ብቻ ነው እንጂ እንደ ተርሞስታት ሙቀቱንም ቅዝቃዜውንም እንዲህ ሆነ በማለት ሰላማቸውን አያስነኩም። እርሱን ትክክል አይደለህም ማድረግ ያለብህን አታውቅም ማለት አይቻልም ና የሚሰራውን ሁሉ ያስተወላልና።
ልጆች በባህርያቸው ሰላማቸው የሚነካ አይደለም። ሰላማቸው እ/ር ነውና። እግዚአብሔር ሰላም ነውና። ሰላም ይሁን ስትሉ እኮ እ/ር ይሁን እያላችሁ ነው። መልካም ይሁን ስትሉም እ/ር ይሁን እያላችሁ ነውና። እ/ር መልካም ነውና። “ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፉ” ሲላችሁ የምታሸንፉበት መለካም ኅይል ሌላ አይደለም እራሱ እ/ር ነው መልካም። በእ/ርም ድል የማትነሱት ነገር የለም። ስለዚህም የእግዚአብሔርን የፍርድ ሂደት ልናስተውል ይገባል። ፍርዱ ሲገለጥ መልካሙን ከክፉ ይለየዋል ከዛም ለጽድቅ የመታዘዝን ጣእም ያቀምሳል በተመሳሳይ ሰአትም ኩፉውን በገዛ ውጤቱ ፍሬውን ለማብላት ነው። በመጨረሻም ለመስበር፤ ለማረም፤ ከዛም ሃጥኡን ለመዋጀት ሲሆን ያንም የሚያደርገው ሐጥያተኛው ከሃጥያቱ ተመልሶ የሰላምንና የህይወትን ጠባብዋን መንገድ እንዲያገኛት ለማድረግ ነው። ያም የእ/ር አራሚ ፍርድ ዳግመኛ በሰፊው የጥፋት መንገድ እንዳይሄድ የልቡን ሸለፈት በመግረዝ ይገራዋል። ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ የእ/ር ድንቅ ስራ ነው።
ታዲያ ይህ ትእይንት የአለም ሲስተም [ባቢሎን(የመገለጡ ደረጃ ይለያያል)]ፍጻሜው በቅርብ ነውን? ክፉዎች እና ባለጌዎች ፤አታላዮች አመፀኞች ወዘተ… እየከፋባቸው እንደሚሄድ ግልጽ ነው። በዛውም ልክ በእኛ ምድርም ላይ ሆነ በሌሎች አገሮች ያለው የእግዚአብሔር ፍርድ በጣም የተስፋፋ እንደሆነ በመንፈስ እናስተውላለን። የእግዚአብሄር ልጆች በክብር መገለጥ እስከ ሚገለጡበት እስከዛ ጊዜ ድረስ የአመፃ ሚስጥሩ በታላቅ ፍጥነት እንደሚጨምር ሳንደናገጥ መጠበቅ አለብን በዚያው ልክ የሚከለክል አለና። ልጅነት የበላይነት እና ስልጣን ይዞ ለፍጥረት መገለጥ የተከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተስፋ ሙሉውን ያስጨብጠናል. “ዮሐንስ ራእይ 2/26-27 ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፥ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፥ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ Rev 2/26 And he that overcometh, and keepeth my works unto the end, to him will I give power over the nations:27 And he shall rule them with a rod of iron; as the vessels of a potter shall they be broken to shivers: even as I received of my Father.”
የእ/ር ሉአላዊነት ሰው ተስማማም አልተስማማ የታወቀ ነው ስለ ሃገራችንም ብዙ ማለት ይቻላል እራሱ የቃሉ ስልጣን ይናገር ብለን ትተነዋል ። የጌታ ፀጋ ከመንፈሳችሁጋር ይሁን።
ወደ ሮሜ ሰዎች 13
1 ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።
2 ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ።
3 ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤
4 ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና።
5 ስለዚህ ስለ ቍጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው።
ምንም ብናደርግ ጉልቻ ቢለዋወጥ.. ነው ነገሩ የስርአት መቀያየር ለውጥ ሊያመጣ አይችልም ብሄራዊ ወይም አገር አቀፍ ንስሃ በእግዚአብሔር ፊት እንጂ።
http://wongelradio.org/ Brother Binyam T. Alemayehu 1/31/2018