የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ
አብዛኛው ሰው ዘመናዩ ከመከራው በፊት መነጠቅ(rapture) የሚለው ንድፈ ሃሳብ ከ200 መቶ ያነሰ እድሜ እንዳለው አይገነዘብም። የዚህ ጽንሰ ሃሳብ የጀመረው በ1812 በስፓኒሽ ቋንቋ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረ ሰው manuel de lacunza y diaz የተባለ በ2 መጽሐፍት እትም 900 ገጽ ስራው “ዘካሚንግ ኦፍ መሳያ ኢን ግሎሪ ኤንድ ማጂስቲ “ በሚለው ተጀመረ ። ቡሃላም በሬቨረንድ edward irving በ1827 ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ታተመ።

ይህ ሃሳብ ያስከተለውን የአመለካከት መዘዝ ወደፊት እንነካካዋለን። በእ/ር ቃልም እሳት እናሳልፈውና አንጥረነው በዚህ ጉዳይ የነጠረውን እውነት ጌታ እንደ ረዳንን መጠን እንይዛለን። ስለ መነጠቅ ከብዙ ወገኖቼ ጋር በጸጋ ለመጠቃቀም በመነጠቅ ሃሳብ ላይ ከዚህ ቀደም ተነጋግሬ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይም ከጥቂቶች በቀር ፈጽሞ ከእ/ር ቃል ጋር የማይጠጋጋ ከአራምባና ቆቦ ይልቅ መራራቅ እዳለው አስተውያለሁ። በዛሬው ጥናታችን እንድናየው የምፈልገው አማኞች ሁሉ ይነጠቁና የማያምኑት መከራውን ሊፋለሙ በዚህ ይቀራሉ የሚለውን አመለካከት ነው።

እነዚህ የተለመዱ አመለካከቶች ከተደገፉባቸው ቃላት መካከል በማቴ 24፡39-41 የሚገኘው ነው። “39 የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። 40 በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ 41 ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች።” በዚህ ቃል ላይ የተለመደው አመለካከት አማኞቹ እንደ ሚወሰዱ እና የማያምኑት እንደ ሚቀሩነው። ጌታ ግን ይህን እያስተማረ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይህን እንድናስተውል ከላይ በቁጥር 37-38 ያለውን እናስተውል። “37 የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። 38 በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥” በቁጥር 37 የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ እንደ ሚሆን ይነግሮናል። በኖህ ዘመን እንደ ነበረ ከሆነ በኖህ ዘመን ምን ይመስል ነበር የሚለው ጥያቂያችን ነው። ዘፍጥረት 7፡13-23 ይገልጽልናል።

“13 በዚያውም ቀን ኖኅ ወደ መርከብ ገባ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም ካም ያፌትና የኖኅ ሚስት ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ገቡ። 14 እነርሱ፥ አራዊትም ሁሉ በየወገናቸው፥ እንስሳትም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም ሁሉ በየወገናቸው፥ ወፎችም ሁሉ በየወገናቸው፥ የሚበሩ ወፎችም ሁሉ፥ 15 ሥጋ ያላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ። 16 ሥጋ ካለው ሁሉ የገቡትም ተባትና እንስት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ እግዚአብሔርም በስተ ኋላው ዘጋበት። 17 የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን ነበረ ውኃውም በዛ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች። 18 ውኃውም አሸነፈ፥ በምድር ላይም እጅግ በዛ መርከቢቱም በውኃ ላይ ሄደች። 19 ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ። 20 ውኃው ወደ ላይ አሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ ተራሮችም ተሸፈኑ። 21 በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ ወፉም፥ እንስሳውም፥ አራዊቱም፥ በምድር ላይ የሚርመሰመሰው ተንቀሳቃሹም ሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ጠፋ። 22 በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት ነፍስ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ። 23 በምድር ላይ የነበረውም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ፥ እስከ ሚርመሰመሰውም ሁሉ ድረስ፥ እስከ ሰማይ ወፍ ድረስ ተደመሰሰ ከምድርም ተደመሰሱ። ኖኅም አብረውት በመርከብ ከነበሩት ጋር ብቻውን ቀረ።”

ከቃሉ እንዳስተዋልነው ጻድቁ ኖህና ቤተሰቡ ነበሩ በምድር የቀሩት ተጠርገው የተወሰዱት ሃጥአን ነበሩ። እ/ር የሃጢያት ጽዋቸው ስለ ሞላ በውሃ አስጥሞ በመግደል ከምድር የወሰደው ሃጥአኑን ነው እንጂ የነጠቀው ጻድቃኑን አልነበረም። በቀደመው ኪዳን መጽሐፍትም ሃጣንን እ/ር በፍርድ ሲነሳ ረጅምን እድሜ ሳይጠግቡ ከምድር እንደ ሚነጥቃቸው የሚያሳዩ ብዙ የእ/ር ቃላት አሉ። ለምሳሌ
መጽሐፈ ምሳሌ 2፡22 ኃጥኣን ግን ከምድር ይጠፋሉ፥ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።
መዝሙረ ዳዊት 50፡22 እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፥ ይህን አስተውሉ አለዚያ ግን ይነጥቃል የሚያድንም የለም።

የሰው ልጅ መምጣት እንደዚህ እንደ ኖህ ዘመን ከሆነ በዚያን ቀን የሚሆነው ብዙዎች እደሚያስቡት ሳይሆን ተቃራኒው ነው የሚከሰተው። ያም አማኞች ወደ ሰማያት ይነጠቃሉ ከዚያም ነጭ ቢጃማ ለብሰው ዘምባባ እያውለበለቡ ምንም ሳይሰሩ ለዘላለም ሊኖሩ እንደሚያስቡት ሳይሆን በኖህ ዘመን እንዳደረገው የማያምኑትን በፍርድ ከምድር እንደ ሚነጥቅ የሚናገር ሃሳብ ነው። ጌታ እየሱስ ይህንን ሃሳብ የሚመስል በዚህ ምእራፍ ላይ ብቻ አይደለም ያስተማረው

“የማቴዎስ ወንጌል 13፡24-30 ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። 25 ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። 26 ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። 27 የባለቤቱም ባሮች ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። 28 እርሱም፦ ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም። እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። 29 እርሱ ግን፦ እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። 30 ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ። 31 ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤”

ከዚህ ቃሉ እንደ ምናስተውለው አማኞች(ስንዴዎች) ከማያምኑት(እንክርዳዶች) ጋር አብረው እንዲያድጉ የመከሩ ጌታ ፈቅደዋል። በጨረሻው የመከር ጊዜ ሲደርስ አጫጆችን ያዘዘው አስቀድማቹሁ እናስተውል አስቀድማችሁ የማያምኑትን(እንክርዳዶችን) ልቀሙ በእሳት ለማቃጠልም በየኖደው እሰሩ ነው ያለው እንጂ ስንዴዎችን አስቀድሙ አይደለም። ይሄም ሌላ ግልጽ ተቃራኒ ምሳሌ ጡንቻ ያወጣውን ገናና የመነጠቅ አስተምህሮትን ሚዛን እንዳይደፋ ያቀለዋል ። ነገሩ ማንም ሲናገር እንደ እ/ር ቃል ይናገር ነውና እውነትን ለመናገር መፍራት የለብንም።

ሌላው ይህን እውነት የሚያጸናው ጌታ በሚቀጥሉት ቁጥሮች ይህንኑ መሚከተለው መልኩ ስለ ምሳሌው ፍቺ ገለጻ መስጠቱ ነው።
“36 በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው። የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት 37 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ 38 መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ 39 እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። 40 እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። 41 የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ 42 ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 43 በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ”

የምሳሌው ገለጻው በአብዛኛው ያተኮረው ለእንክዳዶቹ ምን እንደ ሚደርስባቸው ነው። ተለቅመው ወደ እሳት ባህሩ የተላኩት እነሱ ናቸው። እሳቱን በምንም መልኩ ተረዱት ቅደም ተከተሉ ግን ያ ነው። “ እ/ር የሁሉፈጣሪና ዳኛ” በሚለው መልክት የእሳት ባህሩ ፍቺ “a lake of divine purification የመለኮት የማጣሪያ ባህር” እደሆነ ፍርድ የሚለው ሃሳብ እንደ የተጠበቀ ሆኖ አይተነው ነበረ ። ከጌታ ምሳሌዎች አንድ ነገር ግልጽ ነው ከምድርን የሚወሰዱት አማኞች ሳይሆኑ የማያምኑት ናቸው።
“የሉቃስ ወንጌል 17፡34 እላችኋለሁ፥ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። 35 ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች። 36 ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል።”
እንግዲህ እንደ እነዚህ ያሉ ቃላቶች ፍቻቸው በፊልም እንደ ተሰራው ሳይሆን ከላይ በቃሉ የእውነት ብርሃን እንዳስተዋልነው በመጨረሻው “እንደ ኖህ ዘመን ይሆናል” እንዳለው ነው። ቀሪው በተሰሎንቄ ያለውን ሃሳብ ጨምሮ ጌታ ቢፈቅድ በሚቀጥለው ጊዜ እናየዋለን። ጌታ ይብዛላችሁ አሜን!